- Covenant
አቤቱ አንተ የዘላለም ንጉሥ፣ ብሔረሰቦችን ፈጣሪ፣ እያንዳንዱን ፈራሽ አጥንት ገንቢ የሆንከው ሆይ፣ ክብር ለአንተ ይሁን! ከእነዚያ ከአንተ ከራስህ በስተቀር ከሁሉም ሌላ ነገር ራሳቸውን ከአላቀቁት፣ የገዛ ራሳቸውን ወደ አንተ አቅጣጫ ከመለሱት፣ በአንተ በታዘዙት መከራዎች ወደ ስጦታዎችህ አቅጣጫ ከመዞር ካልተገኙት ጋር እንድትቆጥረኝ፣ የሰው ዘርን በመላ ወደ ግርማህና ወደ ክብርህ አድማስ፣ አገልጋዮችህንም ወደ ፀጋህና ወደ ችሮታዎችህ መንበር በጠራህበት ስምህ እለምንሃለሁ፡፡
ጌታዬ ሆይ፣ የቸርነትህን እጄታ አጥብቄ ይዣለሁ፣ በችሮታህም ካባ ዘርፍ ላይ በጽናት ተንጠላጥዬአለሁ፡፡ ስለዚህ የአንተን ትዝታ በስተቀር የሌላውን የማንኛውንም ሰው ትዝታ ከውስጤ የሚያነፃውን ከቸርነትህ ደመናዎች እንድትልክልኝና ወደ እርሱ የአንተን ቃል-ኪዳን ያፈረሱት፣ በአንተና በምልክቶችህ ያላመኑት ቅዋሜ ቀስቃሾች ሊቃወሙት ወደተሰለፉበት፣ የመላው የሰው ዘር የስግድት ዓላማ ወደሆነው ለመመለስ እንድታስችለኝ እለምንሃለሁ፡፡
ጌታዬ ሆይ በቀናትህ የልብስህን መዓዛዎች፣በገጽህ ብርሃን ውበቶች መከሰቻ ጊዜም የግልጸትህን እስትንፋሶች አትንፈገኝ፤ አንተ የሚያስደስትህን ነገር ለማድረግ ኃይል የተመላህ ነህና፤ ምንም ነገር የአንተን ፈቃድ ሊቋቋም፣ ወይንም አንተ በስልጣንህ የወሰንከውን ሊያስቀር አይችልም፡፡
ከአንተ ከፍጹም ኃያሉ፣ ከፍጹም ጠቢቡ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡
እርሱ ኃያሉ፣ ይቅር -ባዩ ፣ ሩኅሩኁ ነው፤
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አገልጋዮችህን በሲኦልና በስህተት አዘቅት ውስጥ ሆነወው ትመለከታቸዋለህ፣ አቤቱ አንተ የዓለም ፍላጎት ሆይ፣ የመለኮታዊ መርሖ ብርሃንህ ወዴት ነው. አንተ ረዳት ቢስነታቸውንና ደካማነታቸውን ታውቃለህ፤ አንተ የመንግስተ-ሰማይና የምድር ኃይሎች ሁሉ በመዳፉ ውስጥ የሚገኙት ሆይ፣ የአንተ ኃይል ወዴት ነው.
ጌታ አምላኬ ሆይ፣ ከእነዚያ በመጽሐፍህ ውስጥ የሚገኙትን ትዕዛዛትህን ከአከበሩት አንዱ እንድሆን ፈቃድህ ይሆን ዘንድ በፍቅራዊ ደግነትህ ብርሃኖች ውበት ፣ በዕውቀትህና በጥበብህ ውቅያኖስም መትመም፣ የመንግስትህን ሕዝቦች በአሳመንክበትም ቃልህ እለምንሃለሁ፡፡ ለታማኞችህ ለእነዚያ የመለኮታዊ ዕውቀት ብልጭታን ወይን -ጠጅ ከቸርነትህ ጽዋ በመጠጣት ፍላጎትህን ለመፈፀምና ቃል-ኪዳንህንና አዲሱን ሥርትህን ለመጠበቅ ፈጥነው ለተነሱት ያዘዝክላቸውን ለእኔም እዘዝልኝ፤
አንተ የፈለግኽውን ለማድረግ ኃይል የተመላህ ነህና፡፡ ከአንተ ከሁሉን አዋቂው ፣ ከፍጹም ጠቢቡ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡
ጌታ ሆይ፣ አቤቱ አንተ የሰዎች ሁሉ ጌታ ሆይ በዚህና በወዲያኛው ዓለም የሚያበለጽገኝንና ወደ አንተ የሚያቀርበኝን በቸርነትህ እዘዝልኝ፡፡ ከአንተ ከአንዱ ከኃያሉ፣ ክብር ከተመላው በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡
ጌታ ሆይ፣ እርምጃዎቻችንን በመንገድህ ላይ አጠናክርልን፣ ልቦቻችንንም አንተን እንዲታዘዙ አበርታልን፣ ገልፆቻችንን ወደ አንድነትህ ውበት መልስልን፣ ልቦናዎቻችንን በመለኮታዊ አንድነትህ ምልክቶች አስደስትልን፣ የሕያዋን ሁሉ ህልውና በታላቅነትህ ራዕይ ፊትውዳሴህን መዝሙር ይዘምር ዘንድ፣ አካሎቻችንን በፀጋህ መጎናፀፊያ አስጊጥልን፣ ከዓይኖቻችንም ላይ የኃጢአተኛነትን ግርዶሽ ግለጥልን፣ የፀጋህንም ጽዋ ስጠን፡፡ ጌታ ሆይ የፀሎት ቅዱስ የላቀ ሐሴት፣ ከቃላትና ከፊደላት ከፍታ በላይ ከፍ ያለ፣ ከክፍለ -ቃልና ከድምጽ ሁኔታም የመጠቀ ፀሎት -ነፍሶቻችንን ይሞላ ዘንድ፣ ሁሉም ነገሮችም በውበትህ ግልጸት ፊት ፍጹም ወደሌለ- ነገር ይለወጡ ዘንድ፣ ምሕረት በተመላበት ቃላትህና በመለኮታዊ ሕያውነትህ ምስጢር ራስህን ግለጽ፤
ጌታ ሆይ!እነዚህ በቃ ኪዳንህና በአዲስ ሥርዓትህ ጥብቅና ጠንካራ ሆነው የቆዩ፣ የእምነትህን የጽናት ገመድ አጥብቀው የያዙ፣ በታላቅነትህም ካባ ጠርዝ ላይ የተንጠላጠሉ አገልጋዮችህ ናቸው፡፡ ጌታ ሆይ፣ በፀጋህ እርዳቸው በኃይልህም አጠናክራቸው አንተንም እንዲታዘዙ ሽንጦቻቸውን አበርታ፤
አንተ ይቅር ባዩ ፀጋ የተመላው ነህና፤
አቤቱ አንተ ሩህሩህ አምላክ ሆይ! ስለአነቃኽንና እንዳስተውል ስለአደረግኽኝ ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ የሚያይ አይን ሰጠኽኝ፤ የሚሰማ ጆሮም ለገስክኝ፣ ወደ መንግስትህ እንድገባ አደረግኽኝ፣ ወደ መንገድህም መራኽኝ ትክክለኛውን መንገድ አሳየኽኝ፣ ወደ መዳኛ መርከብም እንድገባ አደረግኽኝ፣ አምላክ ሆይ! ጽኑ፣ ጠንካራና የማልበገር እንድሆን አድርገኝ፣ ከኃይለኛ ፈተናዎች ጠብቀኝ፣ በኃይል በተጠናከረው የቃል-ኪዳንህና የአዲሱ ሥርዓትህ ምሽግ ውስጥ ከልለህና ጠብቀህ አኑረኝ፡፡ አንተ ኃይል የተመላው ነህ፡፡ አንተ የሚያየው ነህ፤ አንተ ሰሚው ነህ፡፡
አቤቱ አንተ ሩኅሩኁ አምላክ ሆይ፤ እንደመስታወት በፍቅርህ ብርሃን የሚያንፀባርቅ ልብ ስጠኝ፣ ይህን ዓለም በመንፈሳዊ የፀጋ ጎርፎች አማካይነት ወደ ጽጌረዳ አትክልት ስፍራ ለመለወጥ የሚያስችሉኝን አስተሳሰቦች ለግለሰኝ፡፡
አንተ ሩኅሩኁ፣ መሀሪው ነህ፤ አንተ ታላቁ ቸር አምላክ ነህ፤ አቤቱ አንተ ጌታዬና አለኝታዬ ሆይ! ተወዳጆችህ በኃያሉ ቃል-ኪዳንህ ጽኑ እንዲሆኑ ለግልጹ እምነትህ ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ፣ በብርሃናት መጽሐፍ ውስጥ ያስፈርካቸውን ትዕዛዛት እንዲፈጽሙ፣ የመርሖ ዓርማዎችና የላይኛው ዓለም ጉባኤ ፋኖሶች ወሰን የሌለው ጥበብህ ምንጮች ከከፍተኛው ሰማይ በማብራት በትክክል የሚመሩ ከዋክብት እንዲሆኑ እርዳቸው፤
በእውነቱ፣ አንተ የማይበገረው ፍጹም ኃያሉ ፍጹም ኃይል የተመላው ነህና፤