Ridván Messages
Amharic · Universal House of Justice
ሁለት ብቅ እያሉ ያሉ እውነታዎች እነዚህን ቃላቶች ለእናንተ እንድናካፍል ገፋፍተውናል፡፡ የመጀመሪያው እውነታ
እያንዣበበ ስላለውና አሰቃቂ ስለሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አደጋዎች በዓለም ዙሪያ እያደገ የመጣው ንቃተ-ህሊና ነው። በብዙ አገሮች ውስጥ እልቂትን ለመታደግ ጀግንነት የመላቸውና ቆራጥ እርምጃዎች በጋራ ቢወስዱም ፣ በቤተሰቦች እና በግለሰቦች ላይ ሃዘን በመፍጠር እንዲሁም መላ ማህበረሰቦችን ቀውስ ውስጥ በመክተት ሁኔታው እነሆ ከባድ ሆኗል፡፡ የመከራ እና የሃዘን ማዕበሎች ከቦታ ወደ ቦታ እየተከሰቱ ነው ፤ እናም ይህ በተለያዩ ወቅቶች፣ በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ሀገሮችን ያዳክማል፡፡
ሁለተኛውና በየዕለቱ ይበልጥ ገሃድ እየሆነ ያለው እውነታ፣ የባሃኢ ዓለም ሊታወስ ከሚቻል ግዜ ወዲህ አይቶት
የማያውቀውን ተግዳሮት የመቋቋም ብቃት እና ያልተደቆሰ ሕያውነቱ ነው፡፡ የሰጣችሁት ምላሽ ድንቅ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት በናውሩዝ ክብረ-በዓል ወቅት ወደ እናንተ ስንጽፍ፤ እነኛ ተለምዷዊ የእንቅስቃሴ ዘይቤያቸው የተስተጓጎለባቸው ማህበረሰቦች ያሳዩዋቸው አስደማሚ ባህሪያትን አፅንዖት ለመስጠት ሞክረን ነበር፡፡ ወዳጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥብቅ እየሆኑ የመጡ ገደቦችን እንዲያከብሩ በተጣለባቸው ከዛን ወዲህ ባሉ ሳምንታት ውስጥ በሆነው ሁሉ የአድናቆት ስሜታችን ይበልጥ ጨምሯል። አንዳንድ ማህበረሰቦች በሌሎች የዓለም ክፍሎች ካገኙት ተሞክሮ በመማር፣ ደህንነታቸው አስተማማኝ የሆኑ እና ፈጠራ የተመላቸው በሕዝቦች ውስጥ ያሉትን የህዝብ ጤና ፍላጎቶች ግንዛቤ ማሳደጊያ መንገዶችን አግኝተዋል፡፡ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑት እና ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ለኢኮኖሚያዊ ችግር ለሚዳረጉት ልዩ ትኩረት እየተሰጣቸው ነው፤ ይህን አስመልክቶ በባሃኢ የዓለም የዜና አገልግሎት (Baha'i World News Service) ላይ የሚወጡት ዘገባዎች እየተከናወኑ ካሉቱ ቁጥር ስፍር ከሌላቸው እንቅስቃሴዎች አኳያ እፍኝ አይሞሉም፡፡ እነኚህም፥ በጣም ተፈላጊ የሆኑ መንፈሣዊ ባህሪያትን ለመመርመር ፣ ለማስተዋወቅ እና ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች ይበልጥ እየታገዙ ይገኛሉ። እንደዚህ ያሉ በርካታ ጥረቶች በቤተሰብ ወይም በግል ደረጃ መደረጋቸው እንዳለ ሆኖ፣ ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን ወይም የመገናኛ መሳሪያዎች በሚያስችሉበት ግዜ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን በሚጋሩ ነፍሳት መካከል ልዩ የሆነ የትብብር ስሜት ሆን ተብሎ እየተጠናከረ ይገኛል ፡፡ ለጋራ እድገት በጣም አስፈላጊ የሆነው የህብረተሰብ ኑሮ መስተጋብር አይንበረከክም።
የብርሃን ሠራዊት የማይታክቱ ፊታውራሪዎች የሆኑት ብሔራዊ መንፈሣዊ ጉባዔዎች እንዴት ማኅበረሰቦቻቸውን
በብቃት እንደመሩና እና ለተፈጠረው ቀውስ የሚሰጠውን ምላሸ ቅረጽ እንዳስያዙ በማየታችን መንፈሣችን ከፍ ከፍ ብሏል፡፡ እንደ ሁልጊዜም ሁሉ ፍቅር የተመላበት የአገልግሎት ዓርማን በጀግንነት ካነገቡ አማካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ጠንካራ ድጋፍን አግኝተዋል። መንፈሣዊ ጉባዔዎች በየአገሮቻቸው በፍጥነት ተለዋዋጭ ስለሆኑት ሁኔታዎች ወቅታዊ መረጃ ይኖራቸው ዘንድ በሚገባ እየተከታተሉ ሣለም የዕምነቱን ጉዳዮች ለማስተዳደር፤ በተለይም ምርጫን ማካሄድ በሚቻልባቸው ቦታዎች ይህን ለመከወን አስፈላጊውን ዝግጅቶች አድርገዋል። ተቋማት እና ኤጀንሲዎችም በመደበኛ መልዕክት አማካኝነት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች፣ የሚያረጋጉ ማጽናኛዎችን እና ቀጣይ ማበረታቻን ሰጥተዋል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎችም፣ በማህበረሰባቸው ውስጥ ከሚነሱ የውይይት መድረኮች የሚመነጩ ገንቢ ጭብጦችን መለየት ጀምረዋል፡፡ በናው-ሩዝ መልዕክታችን ውስጥ ይህ የሰው ልጅ ጽናቱን እየተፈታተነ ያለው ፈተና ታላቅ ማስተዋልን እንደሚለግሰው እንደምንጠብቅ የገለጽነው ተስፋ እነሆ ዕውን መሆን ጀምሯል፡፡ መሪዎች፣ ታዋቂ ምሁራን እና ተንታኞች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሕዝባዊ የመወያያ ርዕስነት ርቀው የነበሩ መሠረታዊ ጽንሰ-ሀሳቦችን እና ድፍረት የተመሉ ተስፋዎችን መዳሰስ ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ በአሁኑ ጊዜ ገና የመጀመሪያ ጭላንጭሎች ቢሆኑም የጋራ የንቃተ-ህሊና ወቅት ይመጣ ዘንድ እድል እንዳለ ማሳያ ናቸው፡፡
የባሃኢ ዓለም አይበገሬነት በተግባር ሲገለጥ ከማየት የሚሰማን እፎይታ፣ ወረርሽኙ በሰው ልጆች ላይ በሚያስከትለው
መዘዝ በሚሰማን ሃዘን ለዝቧል። በቃ እንግዲህ፣ ምእመናን እና አጋሮቻቸውም የዚህ ሥቃይ ተካፋይ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ አሁን በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ህዝባዊ የደህንነት መስፈርቶችን ከማክበር አኳያ የሚተገብሩት ከወዳጆች እና አዝማዶች ጋር የመራራቅ ሁኔታ፣ ለአንዳንዶች እስከወዲያኛው ላለመገናኘትም መንገዶችን ይከፍታል፡፡ በእያንዳንዱ ንጋት ላይ፣ ፀሐይ ከመጥለቋ አስቀድሞ ተጨማሪ ሥቃዮችን መቋቋም ግድ የሚል ይመስላል፡፡ በዘለአለማዊ ግዛቶች ውስጥ እንደገና የመገናኘት ተስፋ የሚወዷቸውን በሞት ለሚያጡ መፅናኛ ይሁንላቸው። እነኛ ትምህርታቸው፣ ኑሮአቸው፣ ቤታቸው ብሎም መተዳደሪያቸው ራሱ እንኳ ለአደጋ የሚያጋለጡት ልባቸው እፎይታ እንዲያገኝ እና የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲከባቸው እንጸልያለን። ስለእናንተ እና ስለምትወዷቸው እንዲሁም ስለወገኖቻችሁ ሁሉ ባሃኦላህን እንማጸናለን እንዲሁም በረከቱና ሞገሱን እንለምናለን፡፡
ከፊት የሚጠብቀው መንገድ የቱንም ያህል ረዥም እና አድካሚ ቢሆን ፣ ጉዞውን ለመጨረስ ባላችሁ ጽናትና
ቁርጠኝነት እጅግ ሙሉ እምነት አለን፡፡ የሌሎችን ፍላጎት ከራሳችሁ በማስቀደም፣ ያጡትን መንፈሣዊ ምግብ እንዲመገቡ ለማስቻል፣ እነዛ መልስ ለማግኘት ጥማታቸው የሚበረታውን እርካታ እንዲያገኙ ለማድረግ እንዲሁም እነዛ ዓለም ትሻሻል ዘንድ ለመሥራት የናፈቁት አስፈላጊው እንዲመቻችላቸው ለማድረግ ከተስፋ፥ ዕምነትና እና የልዕልና ማከማቻዎች ትወስዳላችሁ። እንዴት ለተባረከው ፍጹምነት ከተሠጡ ታማኝ ተከታዮች ከዚህ ያነሰ ልንጠብቅ እንችላለን?